የጤና ባለሞያዎችን ከሕሙማን፣ ሕሙማኑን ከባለሞያው እናገናኛቸው

cause-image
  • Started on: 19 aug 2023
  • Closing Date: 19 aug 2024

በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ በአንዱ የመንግስት ሆስፒታል ሔዳችሁ ታውቃላችሁ? እንግዲያውስ አንድ ነገር ላሳያችሁ ተከተሉኝ፡፡ በእነዚህ የመንግስት ሆስፒታል ውስጥ ገና ከበር ገብታችሁ ወደ ካርድ ክፍል ስትሔድ ካርድ ለማውጣት ብዙ ሰው ተሰልፎ ወረፋ ሲጠብቅ አልያም ሲጋፋ ታያላችሁ፡፡ ካርድ ለማውጣት ከጠዋቱ 12፡00 ሔዳችሁ ካርድ የሚወጣላችሁ ከቀኑ 4፡00፡፡ እድል ካልቀናችሁ ደግሞ ወረፋህ ወደከሰዓት ሊዘዋወርም ይችላል፡፡ ትልልቅ ሆስፒታሎች ከሔዳሁ ደግሞ ሪፈር ካልያዛችሁ አትስተናገዱም ተብላችሁ በሕመም እያቃሰታችሁ ልትመለሱ ትችላላችሁ፡፡
ካርድ ወጥቶ ወደሕክምና ክፍል ስትገቡ ሌላ ብዙ ወረፋ ይጠብቃችኋል፡፡ ሕክምና ለማግኘት የሰዓታት ወረፋ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ከቀናችሁ በዛው ቀን በሀኪም ታይታችሁ የላብራቶሪ፣ የራጅ እና የአልትራሳውንድ ትዛዝ ወረቀት ይዛችሁ ወደላብራቶሪ ስትሔዱ ሌላ ሰልፍ፡፡ ከቀናችሁ ናሙና ትሰጡ እና ውጤት ለነገ ትባላላችሁ፡፡ ራጅ ከፍል ስትሄዱ ደግሞ አስር ደቂቃ ለማይፈጅ ራጅ ከ ሳምንት በኃላ ትቀጠራላችሁ፡፡ ከሳምንት በኋላ ተመልሳችሁ ራጅ ከተነሳችሁ በኃላ ራጁ ተነቦ ውጤት እንዲሰጣችሁ ደግሞ ሌላ አንድ ሳምንት ትጠብቃላችሁ፡፡ ከሁለት ሳምንት በኃላ ውጤታችሁ በሙሉ ደርሶ መጀመሪያ ወደታይችሁበት የሕክምና ክፍል ትሔዱና የሰዓታት ወረፋ ጠብቃችሁ ውጤታችሁ በሀኪም ታይቶ መድሐኒት ይታዘዝላችኋል ቀጠሮም ይሰጣችኋል፡፡ መድሐኒት ቤት ሌላ ወረፋ ጠብቃችሁ መድሀኒታችሁን ይዛችሁ ውይ ተገላገልኩ በሚል ስሜት ወደቤት ለመሔድ ስታስቡ ኪሳችሁ ውስጥ የትራንስፖርት ብር የለም፡፡ ምክንያቱም ከገጠር ለሕክምና በሬ ሸጣችሁ ያገኛችሁትን ገንዘብ ለአልጋ እና ለምግብ ከፍላችሁ ጨርሳችኋላ፡፡ እንዳትበደሩ ለሕክምናችሁ ከብዙ ሰው ተበድራችኋል፡፡ መፍትሔ ስታጡ እየፈራችሁ እየጨነቃችሁ እጃችሁን ለምፅዋት ትዘረጋላችሁ፡፡ ስለእግዚያብሔር ለሕክምና ከሀገር ቤት ወጥቼ ገንዘብ አልቆብኝ ነው፣ ብላችሁ ትለምናላችሁ፡፡ እንደምንም ብላችሁ ወደሀገር ቤት ትመለሳላችሁ፡፡

እና ተመልሳችሁ ወደእዛ ሆስፒታል ለቀጠሯችሁ ትሔዳላችሁ ወይስ ሕመሙ ቢገላችሁ ይሻላል?
ይህ የብዙ የገጠር ደሃ ማኅበረሰብ የሕክምና ታሪክ ነው፡፡ ለእዚህ ችግር ዋነኛው ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ ያለ የባለሞያ እና የሕክምና ቁሳቁሶች እጥረት ነው፡፡ በተቃረኒው ብዙ የተመረቁ የጤና ባለሞያዎች ሥራ አጥተው በየቤታቸው ተቀምጠዋል፡፡ ሕመምተኛው የዚህን ያህል በባለሞያ እጥረት በወረፋ ሲሰቃይ ሥራ ያጣ ባለሞያ ደግሞ ቤቱ ተቀምጦ በሥራ እጦት ይሰቃያል፡፡
ድርጅታችን ይህን ችግር በትንሹም ቢሆን ለመቅረፍ የበጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎት ድጋፍ ፕሮጀክትን አቋቁሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በባህር ዳር (ፈለገ ሕይወት አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል)፣ በደብረ ብርሃን (ሀኪም ግዛው ሆስፒታል እና በደብረ ብርሃን አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል) ሲተገብረው ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ በሚዛን አማን (የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሆስፒታል) ውስጥ ሥራው ሊጀመር ነው። ፕሮጀክቱ አዲስ የተመረቁ የጤና ባለሙያዎችን በመመልመል በመንግስት ሆስፒታሎች ውስጥ ይመድባል። በጎ ፍቃደኞቹ ተቀጣሪ ባለሞያዎች የሚሰሩትን ሙሉ ሥራዎች በሞያቸው በሙሉ ሠዓት ይሰራሉ።

ይህ ፕሮጀክት ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት። የመጀመሪያው በበጎ ፈቃደኛ ባለሞያዎችን በመጠቀም የሆስፒታሎችን የባለሞያ እጥረት ማሟላት እና የህሙማኑን እንግልት መቀነስ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጎ ፍቃደኛ ባለሞያዎች ለቅጥር የሚያገለግላቸውን የሥራ ልምድ ደብዳቤ እና የቅጥር እድሎችን እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡
በተጨማሪም፣ ግብዓቶች በሚገኙበት ጊዜ ፕሮጀክቱ ለበጎ ፍቃደኞች በሥራ ቦታ ምሳ፣ የትራንስፖርት ወጪ እና ለበጎ ፈቃደኞች የሥራ ፈጠራ ክህሎት ሥልጠና ይሰጣል።
በገንዘብ እጦት ምክንያት አብዛኛው በጎ ፈቃደኞቻችን ያለምሳ እና ያለትራንስፖርት እየተቸገሩ በመስራት ይገኛሉ፡፡ እስካሁንም ፕሮጀክቱ 1400 ባለሞያዎችን አሳትፏል፡፡
እርሶ ለአንድ ተቸግሮ ለሚያገለግል ባለሞያ የትራንስፖርት ወይም የምሳ ወጪ መሸፈን ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ያቅሞትን ያግዙ!
የአቅሞትን ለእዚህ ፕሮጀክት ድጋፍ ያድርጉ።
የእርስዎ ድጋፍ ለበጎ ፍቃደኞችን የትራንስፖርት ወጪ፣ የሥራ ቦታ ምሳ ወጪ እና የክህሎት ስልጠና ወጪዎች እና ለፕሮጀክት አስተባባሪዎች ደመወዝ እና ለፕሮጀክቱ አስተዳደራዊ ወጪ ይውላል።
የሚችሉትን በመደገፍ ሕመሞተኞችን ከእንግልት እና ጤና ባለሞያዎችን ከሥራ እጦት ይታደጉ፡፡

Collections so far

(Rounded figure - does NOT affect actual money deposited)

ETB 0 of ETB 1,000,000 0%