ፈረንሳይ ጊዮርጊስ

አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ

  • Legal Name: አዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ክ
  • Fundraising Since: 17 feb 2026

በአዲስ አበባ የፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘው የደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ የህንፃ ቤተክርስትያናችን ግንባታ ከተጀመረ ከ 9 ዓመታትን በላይ ተሻገረ::
በእነዚህም አመታት ከመሰረት ጀምሮ የስተራክቸር ስራው በ አባቶች ጸሎት ፣ በ አካባቢው ምዕመናን ልገሳ ተጠናቅቆ የ ፍጻሜ (ፊንሽንግ) ላይ ደርሰናል፡፡
ይህንንም ህንፃ ቤተክርስትያን ቀሪ ስራ በ 1 ዓመት ለማጠናቀቅ ከእግዚአብሔር ጋር አኛ ልጆቹ ለመስራት ተነስተናል፡፡ ለዚህም በዓለም ላይ ካሉ የሰማዕቱ ወዳጆች ገንዘብ መሰብሰብ ይቻል ዘንዳ ይህ ወገን ፈንድ ለመጠቀም ከፍተናል።

አስፈላጊ ከሆነ የቤተ ክርስቲያኑ አመሰራረት እና ታሪካዊ አንደሚከተለው ተጠቅሷል :

+++የደብረ ፀሐይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አመሰራረትና አጭር ታሪክ+++ በቀድሞ አጠራር ፀሃፌ ትዕዛዝ ሰፈር በደርግ ዘመነ መንግስት ከፍተኛ 12 ቀበሌ በቀጠና 1 ብረት ድልድይ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር አካባቢ ቦታ ተመርተው እና ቤት ሰርተዉ የገቡ ምዕመናን በአካባቢያቸው ቤተክርስቲያን ባለመኖሩ ለማቋቋም አስበዉና ይህንኑ ሀሳባቸውን ከግብ ለማድረስ በአካባቢው እድሮች የተዉጣጣ ኮሚቴ ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን አምነዉበት በ 1983 ዓ.ም ከሦስት እድሮች የተዉጣጡ 18 የሚሆኑ ሰዎች በመሰባሰባቸውና ከመካከላቸው 7 አባላትን በኮሚቴነት በመምረጥ የቤተክርስቲያኑን ሥራ ሀ ብለዉ ጀመሩ። ይህ ኮሚቴ ስራዉን የጀመረው ከኮሚቴው አባላት በተዉጣጣዉ 84 ብር ነበር። ኮሚቴው ገንዘብ በማሰባሰብና ጠቃሚ ሃሳቦችን በመቀበል ለቀበሌ 12 ጽ/ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ለጠቅላይ ቤተክህነት እንዲፃፍለት ጠየቀ። ቀበሌዉም ቀና ትብብር በማድረጉ የተፃፈውን ደብዳቤ ከማመልከቻ ጋር ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አቀረበ። ቅዱስነታቸዉም ጉዳዮ በቶሎ እንዲፈፀም ለአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ትዕዛዝ ሰጡ። ከዚህ በኋላ ኮሚቴው ቦታ ለመምረጥ ጥረት ያደረገ ሲሆን ከብዙ ቦታዎች መካከል በአካባቢው አጠራር "ጣጤታ" ትርጉሙ "እምብስ" እየተባለ የሚጠራዉን ቦታ በመምረጥ ለአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ጽ/ቤት አቀረበ። የሃገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ሊቀ ስዮማን ራስ አስረስ ከቦታው ድረስ መጥተው በመስራች ኮሚቴው አማካኝነት እየተዘዋወሩ ሲመለከቱ ልዑል ራስ መንገሻ ስዮም ኮሚቴው ቤተክርስቲያኑን ለመስራት አስበዉ እንደነበር የሚያመለክት በአራቱም አቅጣጫ ያስቀመጧቸው ድንጋዮችና የመስቀል ምልክት ያለባቸዉ ብረቶች በመገኘታቸዉ ይህ ሁኔታ የቦታውን ምርጫ የሚያጠናክርና የእግዚአብሔር ቅዱስ ፍቃድ ሆኖ በመገኘቱ ሥራ አስኪያጁ የቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የፍቃድ ደብዳቤ እንዲፃፍ አደረጉ። ሐሙስ ነሐሴ 23 ቀን 1983 ዓ.ም የአካባቢው ምዕመናን በመተባበር የቤተክርስቲያኑን መቃኞ ለመጀመር የተለያዩ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ጀመረ። ሙያ ያላቸዉ በሙያቸዉ በመሳተፍ 24 ቆርቆሮ የወሰደ የግድግዳዉ ቁመት 2.9 ስፋቱ 2.6 x 2.6 ሜ. የሆነ መቃኞ ተሰራ። ቅዳሜ ህዳር 6 ቀን 1984 ዓ.ም 8 ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም የአድባራት አለቆች ሊቃዉንተ ቤተክርስቲያን የበርካታ አድባራት ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ምዕመናን በተገኙበት የቅዳሴ ቤቱ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ። ከላይ እንደተገለጸው በመጀመሪያ የተሰራው መቃኞ ስፋቱ አነስተኛ በመሆኑ ጥቅምት 1987 ዓ.ም ግድግዳውን በሸክላ በመስራት ተሻሽሏል። ይህም እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ መንፈሳዊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ እግዚአብሔር የደብሩ ሰንበት ት/ቤት አባል የሆነውን ዲያቆን ዳዊት አብርሃምን አነሳስቶ አሁን አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለዉ ህንጻ ቤተክርስቲያን በ1995 ዓ.ም ተጀምሮ በ 1996 ዓ.ም ስራው ተጠናቆ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ጥር 23 ቀን 1996 ዓ.ም በታላቅ መንፈሳዊ ስርዓት ህንፃ ቤተክርስቲያኑ ተመርቆ ታቦተ ሕጉ ወደ ቤተመቅደስ እንዲገባ ተደርጓል። በአሁኑ ሰዓት በዚሁ ህንፃ ቤተክርስቲያን አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ በተሻለ ህንጻ 2000 ካ.ሜ ላይ እየተገነባ ይገኛል።

Image