- Started on: 25 dec 2025
- Closing Date: 24 oct 2026
“አሁንም እንሆ እግዚአብሔር ለመቅደስ የሚሆን ቤትን ትሠራ ዘንድ መርጦሃልና ጠንክረህ ፈጽመው” 1ኛ መ. ዜና 28:10
በታንዛንያ የመጀመሪያዋን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አብረን እንገንባ!
ለረጅም ጊዜ በታንዛንያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕጋዊ እውቅናም ሆነ የራሷ ሕንጻ ቤተክርስቲያን አልነበራትም። በተለያየ ምክንያት ወደ ታንዛኒያ በየጊዜው በመጡ ምእመናን የተደረጉ ጥረቶች ፍሬ አፍርተው የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲሆን በታንዛንያ ዳሬሰላም የመጀመሪያ የሆነውን የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ለመስራት አስፈላጊ ከሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ዋና ዋና ሂደቶችን አልፈን ከታንዛኒያ መንግስት የእውቅና ፈቃድ በማግኘት እንዲሁም በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የሰሜን እና ምስራቅ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል መልካም ፈቃድ፣ መመሪያ እና ቡራኬ መሰረት የታንዛኒያ ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ለመስራት የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥራዎችን ጀምረናል።
ነገር ግን በሀገረ ታንዛኒያ የሚኖረው ምዕመን ቁጥር አነስተኛ እና ጊዜያዊ ሰራተኛ የሚበዛበት በመሆኑ በነዋሪው ምዕመን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ የቦታ ግዥ መፈጸም እና ግንባታ መስራት አስቸጋሪ ሆኖብናል። ስለሆነም እርስዎም በዚህ ታላቅ ታሪካዊና መንፈሳዊ ተልዕኮ እርዳታ እንድታደርጉልን በእግዚአብሔር ስም ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የተወሰኑ ምዕመናን ወደ ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመሄድ የጸሎትና ሌሎች የአምልኮ ሥርዓቶችን (የክርስትና ጥምቀትን ጨምሮ) ሲፈጽሙ እንደነበር ምእመናን ይገልጻሉ ያመለክታሉ።
አብዛኛው ምዕመን በየቤቱ የግል ጸሎት በማድረግ መንፈሳዊ ሕይወቱን ለመምራት ይሞክራል፤ ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ምእመን ደግሞ ከቤተክርስትያን እርቆ ይገኛል።
የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቀደም ሲል በየሳምንቱ እሁድ አዳራሿን ለጋራ ጸሎት በነጻ ትፈቅድ የነበረ ቢሆንም፣ ከመጋቢት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ አዳራሹን ለመጠቀም በቀን 50 ሺህ የታንዛኒያ ሽልንግ እንዲከፈል በመደረጉ፣ ምዕመናን ይህንን ክፍያ እየፈጸሙ በዩቲዩብ የሚተላለፈውን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት በጋራ እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ወቅታዊ የቅዳሴ አገልግሎት፡-
የሥርዓተ አምልኮ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ፣ በተለይም ምዕመናን ቅዱስ ቁርባን እንዲቀበሉና ሕፃናት የክርስትና ጥምቀት እንዲያገኙ ለማድረግ፣ በዓመት ሁለት ጊዜ (በደብረ ዘይት በዓልና በፍልሰታ ጾም ወቅት) ከምሥራቅ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ጋር በመነጋገርና በምዕመናን ሙሉ ወጪ ካህናት ከዩጋንዳ እየመጡ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል።
ይህም ማለት አንድ ልጅ ሲወለድ የክርስትና ጥምቀት የሚያገኘው በእነዚህ ሁለት ጊዜያት ብቻ ነው፣ ምዕመናንም ቅዱስ ቁርባኑን ለመቀበል ቢፈልጉ እነዚህን ቀናት መጠበቅ ግዴታቸው ሆኗል። በእነዚህ ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች (ለምሳሌ በሴቶች ወርሃዊ ልማድ ወይም በሥራ ምክንያት ሌላ ቦታ መሆንን ጨምሮ) አገልግሎቱን ማግኘት ካልተቻለ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ መጠበቅ ግዴታ ነው።
ከዩጋንዳ በሚመጡ ካህናት የቅዳሴና ሌሎች የአምልኮ ሥርዓቶች መካሄድ መጀመራቸው፣ ልጆቻቸውን በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያስጠምቁ ለነበሩ ምዕመናን የተወሰነ እፎይታ የሰጠ ቢሆንም፣ አገልግሎቱ በሚፈለገው መጠንና ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊከናወን አልቻለም።
Copyright 2025 - Wegenfund | Powered by WegenTech