የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም እንርዳ

cause-image
  • Started by: Gosaye Gebramariam
  • For: logo.jpg
  • Started on: 05 jun 2023
  • Closing Date: 30 dec 2023

ስምከ ሕያው ቅዱስ ያሬድ

ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ኢትዮጵያም ባለውለታና ታላቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ቅዱስ አባት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ቅዱስ ያሬድ መምህር ወሐዋርያ፤ መጻሕፍትን በጣዕመ ዜማ የደረሰ፤መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በዜማው ያመሠጠረ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡

የቅዱስ ያሬድ ዜማዎች ለቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ሀገራችን ኢትዮጵያንም በዓለም ስሟን ከፍ አድርገው ከሚያስጠሩ ሀብቶቿ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ያሬድ በክዋኔ ጥበብ፣ በሥነ ውበትና በፍልስፍና አዘምኖ ኢትዮጵያን ከፍ ብላ እንድትታይ አድርጓታል ፡፡ ለዚህም ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ በ ዩኔስኮ በማይዳሰሱ ቅርስነት ያስመዘገበቻቸውና የቅድስት ቤ/ያን ሀብት የሆኑት የመስቀል ደመራና የጥምቀት በዓላትን ያለ ቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ድምቀታቸውን ማሰብ አለመቻሉ ለቅዱስ ያሬድ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ምስክር ነው፡፡ ይሁን እንጅ ቅዱስ ያሬድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውጪ እንደ ሀገር በተገቢው ደረጃ ያልተነገረለትና ያልተዘመረለት ፣ የሚገባውንም ክብርና ዕውቅና ያልተቸረው ታላቅ ሊቅና ቅዱስ ነው፡፡

በመሆኑም ይህ ታላቅ ቅዱስ አባት በተሰወረበት በሰሜን ጎንደር ሀ/ስብከት ለሚገኘው የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ቅዱስ ያሬድና ሥራዎቹን የሚዘክሩ፣ ለትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ፣ ለቅዱስ ያሬድ አስተምህሮ ፣ ለማኅሌት አገልግሎትና ድንቅ ለሆኑት የጥበብ ሥራዎቹ የሚመጥንና ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ሞዴል ሊሆን የሚችል በኢትዮጵያውን ዕውቅ የኪነ ህንጻ ባለሙያዎች ዲዛይን የተደረገ ህንጻ ቤተክርስቲያን ፣የቅዱስ ያሬድ ጸዋትወ ዜማዎችና አጠቃላይ ሥራዎቹን መሠረት ያደረገ የፍልስፍና ፣የሥነ ዉበትና ክዋኔ ጥበብ ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት የልኅቀት ማእከል፣ የአብነት ት/ቤት፣ የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች የሚዘከሩበት ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለጎብኝዎች ምቹ የሆነ ሙዚየምና ቤተመጻሕፍት እና ቋሚ የገቢ ማስገኛ ቋሚ የልማት ሥራዎች ለመስራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ስለሆነም ቅዱስ ያሬድ የሁሉም በሁሉም ቦታ ያለ የኢትዮጵያዉያን ሀብትና ኩራት በመሆኑ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ያን አማኞችና የቅዱስ ያሬድ ልጆች፣ የቅዱስ ያሬድ ወዳጆችና የትሩፋቱ ተሳታፊዎች ይህንን ታሪካዊና ለትውልድ ተሻጋሪ ሥራ እውን ለማድረግ ለሚደረገው ጥረት የበኩልዎትን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና የዚህ ታሪካዊ ሥራ አካል እንዲሆኑ በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳምና በቅዱስ ያሬድ ስም ጥሪ እናቀርባለን፡፡

Collections so far

(Rounded figure - does NOT affect actual money deposited)

ETB 64,471 of ETB 2,000,000 3%